ለምን እንመሳሰላለን ???

June 25, 2021
Posted in Blog
June 25, 2021 admin

ለምን እንመሳሰላለን ???

ለምን እንመሳሰላለን ???

ሰላም ለእናንተ

እኛ ሰዎች በቡድን ውስጥ ስንሆን ለምን ማድረግ ያልፈለግነውን ነገር እናደርጋለን ? ለምንስ ልቡናችን ሌላ ነገር እያሰበ አንደበታችን ተቃራኒውን ይናገራል? መልሳችን የሚሆነው መመሳሰል (conformity) ነው::

እስኪ ስለ መመሳሰል ጥቂት እናውራ፤ ኮንፎርሚቲ (መመሳሰል) በሌሎች ሰዎች ተፅዕኖ ውስጥ በማደር የባህሪ ለውጥ ማምጣት ማለት ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት በ1950 ሶሎሞን አሽ የተባለ ሳይኮሎጂስት አንድ ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ በጥናቱም ላይ የነበሩት ተሳታፊዎች አንድ ካርድ ተሰጣቸው በካርዱ ላይም 3 የተለያየ ቁመት ያላቸው መስመሮች ነበሩበት፡፡ ሁለተኛም ካርድ እንዲሁ ተሰጣቸው በዚህኛዉ ካርድ ላይም ከሶስቱ መስመሮች እና በተጨማሪም አራተኛ አንድ መስመር ቀድሞ ከነበረው ከአንደኛው መስመር ጋር የሚመሳሰል ነበረበት፡፡ ከተሳታፊዎቹ የሚጠበቀው ቀላል ነገር ነበር በሁለተኛው ካርድ ላይ ካሉት ከሶስቱ የትኛው መስመር ከአራተኛው መስመር ጋር እንደሚመሳሰል ጮክ ብለው መናገር ብቻ ጥያቄው ቀላል እንደመሆኑ መጠን በተደጋጋሚ የተጠየቁት ተሳታፊዎች ተመሳሳሳይ መልስ ሰጡ፡፡

ትንሽ ቆይቶ ግን አስገራሚ መልስ መምጣት ጀመረ ይህም የሆነው በጥናቱ ላይ ከተሳተፉት ሰዎች መካከል ሆን ብለው አብዛኛዎቹ በመስመሮቹ ቁመትና ተመሳሳይነት ዙሪያ የተሳሳተ መልስ መመለስ ጀመሩ በዚህም ተፅዕኖ

ያደረበት የመጨረሻው መላሽ በዓይኑ ከሚያየው ይልቅ አብሮ የተሳሳተ መልስ ሰጠ፡፡ ጥናቱም በተመሳሳይ መልኩ ሲቀጥል ተመሳሳይ ክስተቶች በተደጋጋሚ ተፈጠሩ በዚህም 75% የሚሆኑት ተሳታፊዎችም ቢያንስ አንድ ጊዜ ኮንፎርም አድረገዋል ወይም ተመሳስለዋል፡፡

ከሰዎች ጋር ለመመሳሰል ወይም ኮንፎርም ለማድረግ በሳይኮሎጂስቶች ከተጠቀሱ እና ከሚያስገድዱን ሁኔታዎች መካከል
አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት፡-

1 የድርጊቱ ዓይነት (Kind of the task)

ሰዎች ግልፅ ያልሆነ ስራ ወይም በደምብ የማያውቁትን የስራ ዓይነት ሲሰሩ ወይም ሲጠየቁ ለማህበራዊ ተፅዕኖ የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው በዚህም የቡድኑን ወይም የሌሎች ሰዎችን ሃሳብ ለማንፀባረቅ ይገደዳሉ፡፡

2 ቡድናዊ ስምምነት (unanimity of the group)

ሙሉ የቡድኑ አባላት በአንድ ድምጽ ፣ በአንድ ሀሳብ ወይም ድርጊት ስምምነት ላይ የሚደርሱ ከሆነ እና አንተ ከእነሱ የተለየ ሃሳብ ካለህ ለመመሳሰል ብለህ ሃሳብህን ለእራስህ ትውጥና የእነሱን ሃሳብ ታንፀባርቃለህ፡፡

3 የቡድኑ ባህርይ (characteristics of the group)

ቡድኑ ለአባላቶቹ በተለያዩ ዓይነት መንገዶች ሳቢ ሆኖ ከተገኘ የእኛን ሀሳብ ወደጎን በመተው ከቡድኑ ጋር እንወግናለን፡፡ በቡድኑ ውስጥ የሚኖረን ደረጃ (status) ሌላው ለመመሳሰል የሚያስገድደን ነጥብ ሲሆን በዚህም አንዱ አባል በቡድኑ ውስጥ ያለው ደረጃ ከፍ ያለ ከሆነ ለመመሳሰል የሚያደርገው ጥረት የለም በሚያስብል ሁኔታ ዝቅተኛ ነው፡፡ ነገር ግን በቡድኑ ውስጥ ያለው ደረጃ አነስተኛ ከሆነ በአብዛኛው ጊዜ ይመሳሰላል፡፡

4 ግለሰቡ የሚመልስበትበት ሁኔታ (the situation in which a person is responding)

ሰዎች በግላቸው ከሚጠየቁና ሀሳባቸውን እንዲገልጹ ከሚደረጉ ይልቅ ብዘ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ሲጠየቁ የመመሳሰል ዝንባሌያቸው ከፍ ያለ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ወደ እኛ ጉዳይ ስንመጣም ተመሳሳይ ነገር በተደጋጋሚ ሲፈጠር ይስተዋላል ለምሳሌ በስብሰባዎቻችን ላይ ሁለት ሶስት የሚሆኑ ተሳታፊዎች (ሆን ብለው የተቀመጡ ሊሆኑ ይችላሉ) ቅድሚያ ዕድል ይሰጣቸውና ከመድረኩ የተነሳውን ሀሳብ በመደገፍ ሀሳባቸውን ይገልፃሉ ቀሪው ተሳታፊም ቀድሞ በቀረበው ሀሳብ ዙሪያ እየተሸከረከሩ ኮንፎርም ያደርጋሉ ወይም ይመሳሰላሉ፡፡

ሌሎች ቦታዎች ላይም በዕድር፣ በቤተሰብ ስብሰባዎች፣ በቡድን ተሰብስበው በሚወያዩ የስራ ባለደረቦች፣ ከጓደኞቻችን ጋር ….በመሳሰሉት ሰዎች የራሳችንን ሀሳብ ከማንጸባርቅ ይልቅ እንደ መስኖ ውሃ በተቀደደልን መስመር ስንሄድ እንታያለን ይህ ማለት ግን ተመሳሳይ ሀሳቦች የሉንም ማለት እንዳልሆነ ከግምት ውስጥ ማሰገባት ጠቃሚ ነው፡፡

መንግስታዊ ስብሰባዎችንማ ባንመለከት ነው የሚሻለን ምክንያቱም ሰዎች ከራሳቸው ሀሳብ ይልቅ የመድረኩን ሀሳብ እንደ በቀቀን ደጋግመው በማቅረብ ከንፎርም ሲያደርጉ ወይም ሲመሳሰሉ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌም እኔ እንኳን ብዙ የተለየ ሀሳብ የለኝም እገሌ ያለውን ለመደገፍ ወይም አፅንኦት ለመስጠት ነው እና የቀደመው ተናጋሪ እንዳለው በሚል አስተያያቶች ሲጀመሩ ማየት የሁልጊዜ ክስተት እየሆነ መጥቷል፡፡ ስብሰባውም ልክ የአንድ ሰው ጭንቅላት እስኪመስለን ድረስ በሚገርም መመሳሰል ይካሄዳል ፤(ይህ ነገር ግን ከለውጡ በኋላ ነዉ በፊት??

ከላይ ከተገለጹት ነጥቦች በተጨማሪ በእኛ ዘንድ በከፍተኛ ሁኔታ የሚታዩ መመሳሰሎች ምንጫቸው በብዛት ምን ይሉኝን መፍራት (ይሉኝታ) ነው፡፡ በዚህም ይህን ሀሳብ ባቀርብ ምን ይሉኛል ? እንደዚህ ማድረግ ፈልጌ ነበር
ግን ምን ይሉኛል ?. . . . . . ለዚህ ሁሉ ምንጩ ደግሞ ዝቅተኛ የሆነ በራስ የመተማመን ስሜት ነው፡፡
አማራጭ ሀሳቦችን ማቅረብ ትተን የሌሎችን ሀሳብ በመደገፍ የራሳችንን ሀሳብ ወደጎን በመተው ሹፌሩ ብቻ እየነዳ ወደ ራሱ መዳረሻ ያደርሰናል ምክንያቱም የእኔ መዳረሻ እዚህ ነው ብለን መናገር አልቻልንማ… ምክንያቱም የእኛ
መዳረሻ ቀድሞ ተወስኗልና…. ምክንያቱም ከመንጋው ጋር ለመነዳት ተዘጋጅተናልና…….
ሰላማችሁ ይብዛ…..

መልዕክቱን ከወደዱት ለወዳጅ ዘመድዎ ያካፍሉ

WHERE TO FIND US

Nasir Abdu Coffee Exporter

Flip Building, 3rd floor
around Yetebaberut Gas Station
Addis Ababa, Ethiopia

info@nasirabducoffee.com, nasirabdu008@gmail.com

Office Number:
+251-114-629656

Mobile Number:
+251917551677, +251919139151, +251912222843

© 2023
contact-section